የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የህክምና ግብዓት የተሟላላቸው ጽዱ የጤና ተቋማትን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የህክምና ግብዓት የተሟላላቸው ጽዱ የጤና ተቋማትን ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጓል
ባህርዳር ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የህክምና ግብዓት የተሟላላቸው ጽዱ የጤና ተቋማትን ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉ ተመላከተ።
በባህርዳር የሚገኘው የአዲስ አለም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያስገነባው የማስፋፊያ ክፍሎች ግንባታና የግቢ ውበት ተጠናቅቆ ተመርቋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ የክልሉን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋትና አገልግሎቱን ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ እየሆኑ ነው ብለዋል።
በክልሉ ጤናማ ዜጋ ለማፍራት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጤና ተቋማትን በግብዓትና በሰው ሃይል ማሟላት ይገባል ብለዋል።
ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የ25 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማዘመንና የህክምና ግብዓትን ማሟላት ላይ ትኩረት ማድረጉን አመልክተዋል።
ከዚህ ባለፈ የጤና ተቋማትን ጽዱ፣ አረንጓዴና ውብ በማድረግ ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።ይህም እንደ ሀገር የተያዘውን የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱል ከሪም መንግስቱ በበኩላቸው፣ ጽዱ በሆነና ንጽህናው በተጠበቀ ተቋም የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች የተገልጋዩን እርካታ እንደሚጨምሩ ተናግረዋል።
በዚህም የአዲስ አለም ሆስፒታልን ጨምሮ በክልሉ 58 ሆስፒታሎች ለጤና ባለሙያዎችና ለህክምና ፈላጊዎች ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአዲስ አለም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ጸዳሉ ዓለሙ፤ የማስፋፊያ ግንባታው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ከማስፋፊያ ግንባታዎቹ መካከል 14 የጽኑ ህክምና፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ግቢውን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል።