ብልፅግና ፓርቲ ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር! የብልፅግና ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመራር አባላት ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር! የብልፅግና ፓርቲ የዘንድሮው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሪ መልዕክትነት ተሰይሟል።
የብልፅግና ፓርቲ የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ የምርጫ ምልክት የስንዴ ነዶም የመደመር፣ የአንድነትና የትብብር ተምሳሌትነትን የሚወክልና የምርታማነት መገለጫ መሆኑ ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ብልፅግና ከትናንት የሚወሰዱ እሴቶችን በመገንዘብ፣ የሚወረሱትን እና የሚወገዱትን አምዶችን አውቋል።
ከነዚህም በመነሳት አዋጭ የሆነውን የኢትዮጵያ ጉዞ መተለሙን ጠቁመው፤ የብልፅግና የምርጫ ማኒፌስቶ የያዘውም ይህንኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ ምርጫዎች መካከል የተፈጠረው አንዱ እመርታ ዲጂታላይዜሽን መሆኑን አመላክተዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለዲጂታላይዜሽን በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ባከናወናቸው ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
የዲጂታል ፋይናንሲንግ አካታችነት ከማረጋገጥ አኳያ ፓርቲው በተጨባጭ ለማስፋፋት ሰፊ ርብርብ ማድረጉን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ቀጣይነት ያለው በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት ማስፋፋት ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫው መሆኑንም ተናግረዋል።
አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ እርስ በእርሳቸው ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት መጀመሩን አንስተዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን እና አሁን ላይ አገልግሎቱ ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች መስፋፋቱን ጠቁመዋል።
መሶብ በተጀመረባቸው አካባቢዎች የተገልጋዮች እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛው ምሰሶ የሰው ሀብት ልማት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠናን ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል።
ብልፅግናን መምረጥ በዲጂታል ኢትዮጵያ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ኢኒሼቲቮች የተገኙ ውጤቶች ኢትዮጵያውያን ቀና ማለት እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑንም ነው የተናገሩት።