የአፋርን ህዝብ ባህል፣ወግና የዳኝነት ስርዓት በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፋርን ህዝብ ባህል፣ወግና የዳኝነት ስርዓት በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው
ሰመራ፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ የአፋርን ህዝብ ባህል፣ ወግና የዳኝነት ስርዓት በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።
የአፋር ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን (አፋር መድዓ) በመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ያለመ ኮንፍረንስ በሠመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ የአፋር ህዝብ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ያደረሳቸውን ባህል፣ ወግና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይሰራል ብለዋል።
“አፋር መድዓ” የአፋር ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ መተዳደሪያ ስርዓት ሲሆን በማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና የተጣላን የሚያስታርቅ የአብሮነት ዕሴት የሆነ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር መድዓ ዋነኛ ግብ አጥፊን መቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተበዳይ ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ እና በሁለቱ ወገኖች መካከል ዘላቂ እርቅ ማውረድ በመሆኑ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል፡፡
አፋር መድዓን ጨምሮ የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግና የዳኝነት ስነ ስርዓት በማልማትና ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የአፋር ህዝብ ትውፊቱ ሳይበረዝ እዚህ ያደረሰውን ባህላዊ የአስተዳደርና የዳኝነት ስርዓት ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ሚኒስቴሩ እገዛ ያደርጋል።
የለውጡ መንግስት በመደመር እሳቤ መሠረት ባህላዊ ሃብቶችንና ሀገራዊ ቅርሶች አስተማማኝ የልማት ሐይል እንዲሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉና ዓለም ዓቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ከወትሮ በተለየ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የአፋር ባህላዊ ዕሴት የሆነውን “አፋር መድዓ” በዘመናዊ መልኩ ከመጠቀም ባለፈ በሳይንስ ጥናት የተደገፈ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የክልሉ የጎሣ መሪዎችና የሐይማኖት አባቶች እንዲሁም የጅቡቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑካን ቡድን ተገኝቷል።
መርሃ ግብሩ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የዳኝነት ስርዓቱ ከክልሉ አልፎ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑም ተገልጿል።