ቀጥታ፡

በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል

ደብረ ብርሃን፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የገበያ ሥርዓቱን የማዘመን ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በ196 ሚሊየን ብር ያስገነባው 2ኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ተመርቋል።


 

በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል።


 

የክልል መንግስት የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በ7 ከተሞች እየተገነቡ ያሉ የገበያ ማዕከላትም የግብይት ሥርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢብራሂም መሐመድ በበኩላቸው፣ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች  የዜጎችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠርም በክልሉ ስምንት የገበያ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውሰዋል።

እነዚህ የገበያ ማዕከላት ገበያውን በማረጋጋት በኩል ቀጥተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

ከገበያ ማዕከላቱ ባለፈ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ተደራሽነትን በማስፋት የሕብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከተማዋ በፈጣን የዕድገት ጉዞ ላይ እንደመሆኗ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት ወሳኝ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  በድሉ ውብሸት ናቸው።


 

የገበያ ማዕከላቱ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያ በማረጋጋት በኩል ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ አንስተዋል።

በከተማዋ የተገነባው የ2ኛ ደረጃ  የገበያ ማዕከል የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም