ቀጥታ፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ብቁ የሰው ሃይል የሚያፈሩበት ዕድል ተፈጥሯል

ጎንደር ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል የሚያፈሩበት ዕድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ፈርመውታል።


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲያፈሩ የአቅም ግንባታ ላይ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው።

ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ኢንስቲትዩቱ በሚያደርግላቸው ድጋፍ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የመመረቂያ ጥናታቸውን እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ አምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን ማበልጸጉን ጠቅሰው፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርፉን ለጥናትና ምርምር የበለጠ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።


 

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቴክኖሎጂው ለብዝሃ-ዘርፎች ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ጎንደር ዩንቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ ያለውን የካበተ ልምድ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በማስደገፍ የጤና መረጃ ሥርዓትን የበለጠ ሊያዘምን ይገባል ብለዋል።

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በዘርፉ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን ከፍቶ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል።


 

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ለማካሄድ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ዩንቨርሲቲው በሰው ሰራሽ አስተውሎት የምርምር ማዕከል በማቋቋም ከሀገር ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን ግብ ይዞ እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

ስምምነቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ባለፈ ኢትዮጵያ የራሷን ቴክኖሎጂ ማበልጸግ የሚያስችላትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም