ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች አሪቲን በማልማት ተጠቃሚ ሆነዋል

ሳውላ ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ የአሪቲ ተክልን በማልማት እያገኘነው ያለው ገቢ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ የጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ገጠራማው በተለይ በደጋማ አካባቢ የሚበቅለው የአሪቲ ተክል በዓላት ሲመጡ ለጉዝጓዝና ለመልካም መዓዛነት ጥቅም ላይ ይውላል።


 

የአሪቲ ተክልን ከጉዝጓዝ ባለፈም በተለያዩ ዓለማት ክፍሎችም ለባሕላዊና ዘመናዊ ሕክምና ከማዋል ባለፈ መዓዛማ ተክል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለሽቶ መስሪያነት ጥቅም ላይ ይውላል።

 በጎፋ ዞንም ከሚለማው የቅመማ ቅመምና መዓዛማ ተክሎች መካከል አሪቲ አንዱ ነው።


 

በዞኑ ኮረሪማ፣ በርበሬ፣ ሚጥሚጣና ሌሎች የቅመማ ቅመምና የሰብል ምርቶችን በማልማት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ይገኛል። 

በወረዳው በአካባቢ ጥበቃ በለማ መሬት ላይ የአሪቲ ተክልን እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮች እንደሚሉት በአሪቲ ምርት ላይ ተሰማርተው በሄክታር እስከ 16 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል።

አርሶ አደር ፍጹም ጨሌ በዛላ ወረዳ የዳዳ ገላይሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፤ የአሪቲ ተክልን በዓመት ሶስት ጊዜ እያለሙ ይገኛሉ። 


 

በነዚሁ ጊዜያት በሶስት ሄክታር መሬት ላይ የሚያለሙትን የአሪቲ ተክል ለገበያ በማቅረባቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ እንደረዳቸው ገልፀዋል።

በሚያገኙት ገቢም ቤተሰባቸውን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር መሰረት እንደሆናቸው አስረድተዋል።

በሄክታር 16 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ የሚገልጹት አርሶ አደሩ በኩንታል ከ1 ሺህ 600 እስከ 2 ሺህ ብር ድረስ ገቢ እንደሚያገኙም ገልጸዋል።

የገልተሜ ናንቴ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በላይ በርገኔ በበኩላቸው፤ ባላቸው አንድ ሄክታር ማሳ ላይ አሪቲን በማልማት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።


 

ምርቱን ለገበያ በማቅረብ በሚገኘው ገቢም ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እንደቻሉም ነው ያነሱት።

አሪቲ አንዴ ከተተከለ እና ምርቱን በአግባቡ መንከባከብ ከተቻለ የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ምርቱ ተጨማሪ ገቢን ለማግኘት አስችሎኛል ብለዋል።

ምርቱን በተገቢው መንገድ በመንከባከብም በሄክታር እስከ 16 ኩንታል ምርት እንደሚሰበስቡም ነው ያመለከቱት።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የቅመማ ቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑርአዲስ አደም በበኩላቸው፤በዞኑ ከ8 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በአሪቲ ተክል መልማቱን ተናግረዋል።


 

በዚሁ በአሪቲ ተክል ከተሸፈነው መሬትም በዓመት 8 ሺህ ቶን ምርት እንደሚሰበሰብና ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እንደሚቀርብ ገልፀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም ከ2 ሺህ ቶን በላይ የአሪቲ ምርት ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳና ሳዑዲ አረቢያ ገበያዎች መላኩን ተናግረዋል።

የአሪቲ ምርት ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በስፋት እየለማ ሲሆን ምርቱንም በአብዛኛው የሽቶ ፋብሪካዎች እንደሚረከቡት ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም