ቀጥታ፡

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ከ112 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል

መቱ ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦በኢሉአባቦር ዞን በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ከ112  ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የኢሉአባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድጠሃ አባፊጣ፣ የዞኑ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማፋጠን የሚያግዝ መሆኑን ተገንዝበው መታወቂያውን እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል መታወቂያ በቴክኖሎጂው የእድገት ዘርፍ ከተያዙ ሀገራዊ አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑን አስታውሰው ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች መታወቂያውን እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ከ164 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች መታወቂያውን እንዲያገኙ ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ ከ112 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ለስኬታማነቱ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከባንኮችና ከኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በዞኑ ሁሉም ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ መያዝ እንዲችሉ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የዲጂታል መታወቂያ አንድ ሰው አንድ ማንነት ብቻ እንዲኖረው በማድረግ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።


 

የዲጂታል መታወቂያ ለሁሉም ዜጎች ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመንግስት የሚከናወኑ ልማቶች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም