ቀጥታ፡

የመንግስት ሁለንተናዊ ድጋፎች የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ያለውን ተወዳዳሪነት እያሳደገው ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ለቡናው ዘርፍ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገው የዘርፉ ላኪዎች ገለጹ። 

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተፈላጊነት እየጨመረ ከመምጣቱ በላይ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች እየጨመሩ ይገኛሉ።


 

ይህንን ተከትሎም ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 469 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች።

ይህም በሀገሪቱ የቡና ታሪክ ከፍተኛው የገቢ መጠንና የጥራት ደረጃ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ መንግስት ይህንን ውጤት በማስቀጠል በያዝነው ዓመት የሚገኘውን ገቢ ወደ ሦስት ቢሊየን ዶላር ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የቡና ላኪዎች እንደገለጹት፤ በቡናው ዘርፍ እየመጣ ላለው ዕድገትና ስኬት የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ 


 

የታደሰ ደስታ ስፔሻላይዝድ ኮፊ ኤክስፖርት ዳይሬክተር ገብረመስቀል ሃይሉ እንዳሉት፤ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት የኢትዮጵያ ቡና ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ቻይና አልፎ በሁሉም የዓለም ክፍሎች ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል።

በዚህም የድርጅታቸው የደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አረጋግጠዋል፡፡


 

ቀደም ሲል ጥቂት የነበሩ የቡና መዳረሻዎች አሁን ላይ በስፋት መጨመራቸውንና ከዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚመጣው ግብረ-መልስ እጅግ አዎንታዊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትራኮን ትሬዲንግ ኮፊ ሶርሲንግ ማናጀር ሳሚ ኤሊያስ ናቸው፡።

በተለይም መንግስት ለመሬት አቅርቦትና ለወጪ ንግድ ሂደቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ ላኪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ አግዟቸዋል ብለዋል።


 

የኤማ ኮፊ መስራችና ስራ አስኪያጅ መውሃ ሰይድ በበኩላቸው፤ ቡናን በጥራትና በብዛት ማቅረብ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት እያደረገ ያለው የፋይናንስ ድጋፍ ስራቸውን እንዳቀለለላቸውና ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ላኪዎቹ በቀጣይም ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግስት እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም