የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፍትሃዊነት እና አብሮ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፍትሃዊነት እና አብሮ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ ነው
ድሬዳዋ፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፍትሃዊነትና አብሮ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ሐይሉ ተናገሩ።
የባህር በር ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ዕድልን ከማስፋቱ ባሻገር የአንድ ሀገር ዳር ድንበር እንዲከበር ያለው ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም።
ይሁንና እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ባለማስገባት ኢትዮጵያ በተፈጸመባት በደል ከባህር በር እንድትርቅ የተደረገበት ሁኔታ በዝምታ ዓመታትን የዘለቀ ነገር ግን በብዙዎች ዘንድ ቁጭት አሳድሯል።
በመሆኑም አሁን ላይ ዝምታው ተሰብሮ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የትውልድ ጥያቄና የሀገር የህልውና ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ሐይሉ፤ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ላይነጣጠሉ መልክዓ ምድር፣ ተፈጥሮና ታሪክ ያጋመዳቸው ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያለ ቀይ ባህር በብዙ መመዘኛዎች ህልውናዋ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑን ሁሉም የሚገነዘበው እውነታ መሆኑን አንስተው የባህር በር ባለቤት መሆኗ የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፍትሃዊነትና አብሮ የማደግ መርህን መሰረት ያደረገ በመሆኑ አጠቃላይ የቀጣናው ሀገራት ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ በጋራ ሊቆሙ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አሁን ላይ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ መነሳቱ በዓለም አቀፍ ህግ፣ በታሪክም ይሁን በመልክዓ ምድር ተገቢነትን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግ፣ በሰላማዊ ድርድርና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተገቢው ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።