ቀጥታ፡

የዲጅታል ኢትዮጵያ መተግበር የፋይናንስ ስርዓቱን በማዘመን ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ ነው

አርባምንጭ፤የካቲት 3/2018 (ኢዜአ:-የዲጅታል ኢትዮጵያ መተግበር የፋይናንስ ስርዓትን በማዘመን ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን የፋይናንስ ዘርፍ አመራሮችና ተገልጋዮች ገለጹ።

ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተደረጉ ጥረቶች ዘመናዊ አሰራርና ፈጣን አገልግሎት በማስፈን ለሀገራዊ ዕድገቱ ጉልህ ሚና እንዲጫወት እያደረገ ይገኛል።

የፋይናንስ ዘርፍ አመራሮችና ተገልጋዮች እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ መርሃ ግብር የፋይናንስ ስርዓትን በማዘመን ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ጉጆ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የዲጂታል አሰራሩ የፋይናንስ አገልግሎትን በማቀላጠፍ በዜጎች አኗኗር ላይ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል።

የዲጂታል አገልግሎቱ በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ፋይናንስ ተቋማት ሳይመጡ ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን ለማግኘት እንዲችሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ የንግድ ምዝገባ ማድረግ፣ የንግድ ፈቃድ እድሳትና ሌሎች አገልግሎቶች በዲጂታል ስርዓት እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት 6 ወራት ከ107 ሺህ በላይ የንግድ ፈቃድ የታደሰ ሲሆን ከእነዚህም ከ57 ሺህ በላይ የሚሆኑት በኢ-ትሬድና በወረዳ ኔት አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል።

በክልሉ ባሉ 12 ዞኖችና 3 ሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች የሚገኙ ነጋዴዎች በተፈጠረው የዲጂታል ስርዓት ዜጎች ካሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻሉ በርካታ ችግሮችን መቅረፉን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ማርቆስ በበኩላቸው፥ "ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን እንዲሆን የፋይናንስ ሴክተሮች አገልግሎት መዘመን አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

ከ87 በመቶ በላይ የባንኩ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በዲጂታል ስርዓት ውስጥ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ ባንኩ ባዘጋጃቸው የተለያዩ የክፍያ አማራጮች ተጠቅመው፥ ደንበኞች ቤታቸው ወይም ስራ ቦታቸው ሆነው አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

በሞባይል ባንኪንግ በመታገዝ ደንበኞች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው እንዲሁም በኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት የግልና የመንግስት ድርጅቶች ግብይትና ለሰራተኞቻቸው ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

የደንበኞችን ብሔራዊ መታወቂያ ከባንኩ ስርዓት ጋር በማቆራኘት አስተማማኝ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑንም አቶ ደረጀ አስረድተዋል።

የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝ ማድረጋቸው ከወጪና እንግልት ታድጎናል ያለው ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሀርዲዶ ዶሎቦ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም