ማዕከሉ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረውን የጥናትና ምርምር ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረውን የጥናትና ምርምር ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ቋሚ ኮሚቴው
ጂንካ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ) :- የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት እና የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረውን ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የጥናትና ምርምር ስራዎችን ተመልክተዋል።
አባላቱ በአፈር ላይ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር፣ የመኖ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ ዶሮ እንስሳትና ዓሳ እርባታ፣ የሰብል ምርምርን ጨምሮ በምርምር ማዕከሉ የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ተመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ አጉ ዱባን፣ ማዕከሉ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
በተለይም በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉ ጸጋዎች ላይ በማተኮር የእንስሳት እና የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራ እያካሄደ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
የምርምር ማዕከሉ ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ለአርብቶ አደሩ በሳይንሳዊ ጥናት የታገዘ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በአርብቶ አደሩ አካባቢ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የድጋፍና ክትትል ስራው ይጠናከራል ብለዋል።
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ተክሌ ዮሴፍ (ዶ/ር) ማዕከሉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ የሰብልና የእንስሳት ምርታማነትን ለመጨመር እየሰራ ይገኛል ።
በዚህም በማዕከሉ በሰብልና በእንስሳት እርባታ ላይ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች በአርሶና በአርብቶ አደሩ አካባቢ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የምርምር ማዕከላት ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እገዛ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል ።
በተለይ እንደ ሀገር የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለማሳካት በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ ለማድረግ የምርምር ማዕከላት ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርብቶ አደር አካባቢ ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ተክለዮሐንስ ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት የጥናትና ምርምር ስራዎች ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል ።
በምርታማነታቸው የተረጋገጡ አዳዲስ የሰብልና እንስሳት ዝርያዎች ማፍለቅ፣ ማላመድና ምርት መስጠት የማይችሉ አሲዳማ መሬትን በኖራ የማከም እና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።