ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን − የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላችንን እንወጣለን − የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች
ወላይታ ሶዶ ፤ የካቲት 3/2018 (ኢዜአ):- ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን ለማካሄድ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሰራ ነው።
ምክክሩ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና ከዚህ ቀደም ያልተሄደበትን የቆዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ አካሄድ እንደሆነም ታምኖበታል።
ኮሚሽኑም በአሁኑ ወቅት አሳታፊ በሆነ መልኩ በተለያዩ አካላት የሚነሱ አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የማጠቃለያ የምክክር ምእራፍ ላይ መድረሱ ይታወቃል።
ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር ተያይዞም ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ዞን ሀገር ሽማግሌዎች፤ ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ማሕበረሰቡን በማወያየትና ግንዛቤን በመፍጠር ለስኬታማነቱ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የወላይታ ሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰይፉ ለታ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያውያን መካከል ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የመወያየት፣ የመመካከርና አብሮ የመኖር እሴትን ለማስቀጠል ምክክሩ አስፈላጊ ነው።
በአሁኑ ወቅት በተለያየ ምክንያት እየተሸረሸረ የመጣውን ይህንኑ የቆየ እሴት ለማስቀጠል ምክክር ማድረግ ምትክ የማይገኝለት ጉዳይ ነው ያሉት።
መንግስትም ይህንኑ በመገንዘብ በዜጎች መካከል ምክክሮችን በማካሄድ የተፈጠሩ ችግሮችን በውይይትና በመተማመን እንዲፈቱ እያከናወነ ያለው ተግባር በሀገሪቱ ሰላምን ለማጽናት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ሁላችንም መጠሪያችን አንዲት ኢትዮጵያ ናት ያሉት አቶ ሰይፉ "በአንድነት ሰርተንና ለምተን የሀገራችንን ከፍታ ለማረጋገጥ ችግሮቻችንን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እናምጣ" ሲሉም መክረዋል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን የብሔርና የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን ተከባብረን ተዋደን ለዘመናት የመኖር ድንቅ ባህል ያለን ህዝቦች ነን" ይህንኑ ማስቀጠል ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ አብርሃም ባቾሬ ናቸው።
በወላይታ "አዋሲያ"፣ "ሲጋ" እና "ጭማቴታ" የተሰኙና ችግሮች ሲፈጠሩ ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውሉ ባህላዊ እሴቶች ያሉ መሆኑን አንስተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ለኮሚሽኑ ስራ ስኬታማነት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተው በቤተሰብ፣ በጎረቤት ፣በዕድርና በእምነት ተቋማትም ጭምር ግንዛቤ የመፍጠራ ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሮችን በሰከነ ፣ ህዝብን ባማከለና የሁሉንም ድምጽ ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ውይይቶችንና ምክክሮችን ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል አቶ ዳንኤል ደሳለኝ ናቸው
መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ኮሚሽኑ በይፋ ወደስራ በመግባቱ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ያደሩ ቁርሾዎች ለማስወገድ ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠልም ውይይቶችንና ምክክሮችን ለማድረግና ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱም ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም ነው ያረጋገጡት።