የአፍሪካ ሀገራት ቀውስን የሚቋቋሙበት የፋይናንስ ቋት መዘርጋት ይገባቸዋል-የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት ቀውስን የሚቋቋሙበት የፋይናንስ ቋት መዘርጋት ይገባቸዋል-የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፡-የአፍሪካ ሀገራት ቀውስን የሚቋቋሙበት እና ተጋላጭነትን የሚቀንሱበት ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦት ቋት እንዲፈጥሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚን አስመልክቶ የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሳዑዲ አረቢያ አሉላ ከተማ ተካሂዷል።
ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች “የዓለምን የፋይናንስ የድጋፍ ቋትን በማጠናከር፤ ሀገራት ከቀውስ የሚያገግሙበት ፈጣን እና ተአማኒ ፋይናንስ ማቅረብ” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ ከፍተኛ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
በምክክሩ ላይ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አርሜኒያ፣ ግብጽ፣ ፓኪስታን እና ኳታርን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ማዕከላዊ ባንኮች ገዥዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የአፍሪካ ሀገራት በዓለም የፋይናንስ ሴፍቲኔት (GFSN) የሚያገኙት የፋይናንስ አቅርቦት የተገደበ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት ሀገራት በራሳቸው ክምችት እና የአይኤምኤፍ ድጋፍ ላይ ብቻ እንዲወሰኑ ማድረጉን አመልክተዋል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የውጭ ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ቀጣናዊ የፋይናንስ መዋቅሮች በመፍጠር እና ከዓለም የፋይናንስ ቋት ጋር በማስተሳሰር ተጋላጭነትን በጋራ ለመቀነስ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የባንኩ ገዥ ወቅታዊ የዓለም እውነታዎችን በመቃኘት በአዲስ መልክ የተሻሻለውን የአይኤምኤፍ የኮታ ስርዓት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ ያላትን የኢኮኖሚ ጥንካሬ እና እየተተገበሩ ያሉ መዋቅራዊ ሪፎርሞች ከግምት ውስጥ በመክተት የፋይናንስ ኮታ እንዲጨምር ጥሪ ማቅረባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።