ቀጥታ፡

የጎንደር ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ተዘጋጅተዋል

ጎንደር፤ የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፡- በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ገለጹ፡፡

ምርጫ ዜጎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመረጡት ፓርቲ ስልጣንን በውክልና የሚሰጡበት የፖለቲካ ሥርዓት መገለጫ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች አመላክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች እንዳሉት፤ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የዜጎች ተሳትፎ የሚረጋገጥበትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረት የሚጣልበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

ወጣት ሞገስ አራጋው እንደገለጸው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የጎላ ሚና አላቸው።

በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና የዜጎችን ኑሮ አንዲያሻሽሉ ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ የሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀቱን አመልክቷል።

ወጣት ወንድማገኝ ሽመልስ በበኩሉ ለሀገሪቷ ሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምርጫ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግሯል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ አመኔታን ያተረፈ እንዲሆን የድርሻዬን እወጣለሁ ብሏል።

ወጣቱ ትውልድ የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆኑ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሀገሪቷን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ሃላፊነቱን ሊወጣ አንደሚገባ ነው ያነሳው።

በኢትዮጰያ የተጀመሩ የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ጠቅላላ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ ሊካሄድ ይገባል ያለችው ደግሞ ወጣት መጽሄት ተከለወይን ናት። 

በጠቅላላ ምርጫው በመምረጥ በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብቷን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗንም ነው የገለጸችው።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ/ም የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም