በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ
አዲስ አበባ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት የአፈፃጸም ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የበረራ አድማስ ለማስፋት በፖርቹጋል ፖርቶ፣ ቬትናም ሃኖይ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ሶስት ከተሞች ዓለም አቀፍ መዳረሻ መክፈቱን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን አየር መንገድ የከፈታቸው አዳዲስ የዓለም አቀፍ መዳረሻዎችም የበረራ መዳረሻውን ከ145 በላይ ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
በሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቶችን ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራትም የያቤሎ አየር ማረፊያ ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ የመዳረሻ አገልግሎቱን ወደ 23 ማሳደግ እንዳስቻለ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ተጨማሪ ሰባት አውሮፕላኖችን በማስመጣት የአየር መንገዱን አውሮፕላኖች ብዛት 147 ማድረስ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በመንገደኞች ማጓጓዝ ሥራም በስድስት ወራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 10 ነጥብ 64 ሚሊየን ሰዎችን በማጓጓዝ የገቢ አቅሙን ማሻሻል ያስቻለ ስኬታማ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።
በዚህም በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በዕቅድ ከተያዘው አኳያ የሁለት በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት አፈፃጸም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ14 በመቶ ብልጫ መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
ከአንድ ወር በፊትም የግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የግንባታ ሥራው በይፋ መጀመሩን አስረድተዋል።