ቀጥታ፡

ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ለሀገር-አቀፍ ፈተናው የተሻለ ዝግጅት ለማድረግና የላቀ ውጤት ለማምጣት ያግዛል

ሰቆጣ ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፡-ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ለሀገር-አቀፍ ፈተናው የተሻለ ዝግጅት ለማድረግና የላቀ ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑን የሰቆጣ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ገለጹ።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በሰቆጣ ያስገነባው ''ሰላም የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ሰማዕታት መታሰቢያ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት'' ትናንት መመረቁ ይታወሳል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰቆጣ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ግንባታ የበለጠ እንዲያነቡና ተጨማሪ ዕውቀት እንዲታጠቁ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል። 

የ12ኛ ክፍል ተማሪው ሳህለጊዮርጊስ ደባሹ በከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ-መጻሕፍት ባለመኖሩ በክፍል ከሚሰጣቸው ትምህርት ውጭ ተጨማሪ መጽሐፍት ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሷል።


 

የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት ለአገልግሎት መብቃት ዘመኑ የሚጠይቀውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲገበዩና ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል ነው ያለው።

ዘንድሮ ለሚወስደው ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ዝግጅት ለማድረግና የላቀ ውጤት ለማምጣትም የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጿል።


 

ተማሪ እሌኒ ቢምረውና ተማሪ አዱኛ ንጉሴ በበኩላቸው ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ የሚፈልጉትን መጽሐፍት በቀላሉ በማግኘት ራሳቸውን እንዲያበቁ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመደበኛ ትምህርት ባለፈ ለጠቅላላ ዕውቀት የሚሆኑ አባሪ መጽሐፍትን በማንበብ የዕውቀት አድማስንና እይታን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል። 


 

የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ መክብብ እንዳሉት የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

ተማሪዎች አስፈላጊውን አጋዥ መጽሐፍት በቀላሉ እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባለፈ ሀገር አቀፍ ፈተናውን በብቃት እንዲወጡና የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የሰራዊት አባላት በ70 ሚሊዮን ብር በሰቆጣ ከተማ ያስገነቡት የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍትን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በይፋ መመረቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም