ማንችስተር ዩናይትድ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል።
በዕለቱ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በለንደን ስታዲየም ዌስትሃም ዩናይትድ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ምሽት 5 ሰዓት ከ15 ላይ ይጫወታሉ።
ዌስትሃም ዩናይትድ በ23 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ማንችስተር ዩናይትድ በ44 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ያሸነፈው ዌስትሃም ዩናይትድ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል።
በጊዜያዊው አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ ያለፉትን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፏል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እያደረገ ባለው ብርቱ ፉክክር ሶስት ነጥብ እጅጉን ወሳኝ ነው።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ እየተፎካከረ የሚገኘው ዩናይትድ በሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ማንችስተር ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው እ.አ.አ በ2023/24 የውድድር ዓመት ነው።
ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። የ43 ዓመቱ ሳይመን ሁፐር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ ምሽት 4 ሰዓት ከ30 ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቼልሲ በ43 ነጥብ አምስተኛ፣ ሊድስ ዩናይትድ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከኒውካስትል ዩናይትድ እና ኤቨርተን ከቦርንማውዝ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ።