ቀጥታ፡

ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በምርጫ እንዲሳተፉ በማድረግ አካታችነቱን ማረጋገጥ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፡- ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በምርጫ እንዲሳተፉ በማድረግ አካታችነቱን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ አካታችነት እና አሳታፊነት ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል ፡፡


 

በምክክር መድረኩ የክልሎች የሴቶችና ማህበራዊ ዘርፍ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ አደረጃጀት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ ለፍትሃዊ ውክልና እና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። 

በተለይም የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ በማሳተፍ አካታችነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ለዘላቂ ሰላም አዎንታዊ ሚና እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፤ ሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ  ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ  መሆኑን ገልፀዋል።

ምርጫው ነፃ፣ ፍትሀዊ፣ አካታችና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሚና ይጠይቃል ብለዋል።

አካል ጉዳተኞችም በዲጂታል የምዝገባ ስርዓት እንዲመዘገቡ ሁኔታዎችን ምቹ የማድረግ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም