ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የልማት አጋሮች በአካታች እድገት እና ዘላቂ ሰላም ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦‎ ኢትዮጵያ እና የልማት አጋሮች በአካታች እድገት እና ዘላቂ ሰላም ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች ቡድን (DPG) በጋራ ያዘጋጁት ከፍተኛ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በፎረሙ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የልማት ኤጀንሲዎች እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።


 

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የልማት አጋሮች ያላቸውን አጋርነት በአዲስ መልክ በማደስ አካታች እድገት፣ ዘላቂ ልማት እና ሰላምን ማረጋገጥን ያለመ ነው።

ሀገራዊ ምክክር እና የሰላም ግንባታ ሂደትም ምክክር ተደርጎባቸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ያነሱ ሲሆን በሀገሪቱ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማረጋገጥ ሪፎርሙ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው እ.አ.አ በ2024/25 ኢትዮጵያ 9 ነጥብ 2 በመቶ አድገት ማስመዝገቧንና ይህ እድገት እ.አ.አ 2025/26 10 ነጥብ 2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት አመልክተዋል።

ለዘላቂ ልማት አይበገሬነት፣ ማህበራዊ መስተጋብር እና ስትራቴጂካዊ ዓለም አቀፍ አጋርነቶች ወሳኝ መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በውይይቱ ላይ ሀገራዊ ምክክር እና የሰላም ግንባታ ጥረቶች ያላቸውን ሚና አንስተዋል።

የታጣቂዎች ተሃድሶ (ዲዲአር)፣ የሽግግር ፍትህ እና የዜጎች ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ሪፎርሞችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለ32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እያደረገች ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ጉባኤው ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት እና የአፍሪካን የአየር ንብረት አጀንዳ የበለጠ ለማራመድ የሚያስችል መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ እድሎችን ለማስፋት እና ሁሉንም ዜጋ አካታች የሆነ እድገት እንዲመጣ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም