ቀጥታ፡

በአፍሪካ የግብርና ሽግግርን ለማሳለጥና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የውሃና የንጽህና አጠባበቅ ስርዓትን ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፡- በአፍሪካ የግብርና ሽግግርን ለማሳለጥና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የውሃና የንጽህና አጠባበቅ ስርዓትን ማሳደግ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ገለጹ፡፡

በአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህል ምክር ቤት "የአጀንዳ 2063 ግቦች ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ" የሚለውን የሕብረቱ መሪ ሀሳብ በተመለከተ የሲቪል ማህበረሰብ ቅድመ ስብሰባ አካሂዷል፡፡


 

በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ "የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ" የሚለው የሕብረቱ መሪ ሀሳብ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ውሃ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ የተሻለ ነገር ያስፈልጋታል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ዜጎች በተለይም ወጣቶች፣ ሴቶችና የገጠር ነዋሪዎች፣ በግብርና ምርታማነት፣ ጤና እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ንጽህና እየተፈተኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካውያን ያላቸውን የውሃ ሀብት በራሳቸው ጠብቀውና አልምተው መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የሕብረቱ አባል ሀገራት፣ የአጋር ድርጅቶችና የዜጎች ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለማህበረሰቡ ባላቸው ቅርበት ወሳኝ ስትራቴጂያዊ አጋሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤  ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ውሃ ለገጠር ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ ዕድገት፣ ለብሉ ኢኮኖሚ፣ እና ለግብርና ምርታማነት የጀርባ አጥንት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ አባል ሀገራት ዘላቂ ፋይናንስ መመደብና ተጠያቄነትን ማስፈን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት በአሕጉሪቱ የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ንጽህናን በማረጋገጥ የአጀንዳ 2063 ግብ ለማሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህል ምክር ቤት ከፍተኛ መሪ /Presiding Officer/ ሉዊስ ቼክ ሲሶኮ አፍሪካ በቂ የውሃ ሀብት ቢኖራትም ሚሊዮኖች የውሃና የንጽህና አጠባበቅ ፈተና ተጋርጦባቸዋል ብለዋል፡፡

በውሃና የንጽህና አጠባበቅ ለበሽታ ተጋላጮች፣ ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ታዳጊዎች እንዳሉ በማንሳት፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ይሄንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን በማንሳት፤ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

የኢንክሉድ መድረክ /INCLUDE Platform/ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አኒካ አልታፍ ውሃን የተሟላ የንጽህና አጠባበቅ ለእድገት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህል ምክር ቤት የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አመራር፣ ስርዓትና መረጃን በማቀናጀት በቴክኖሎጂ የታገዘ አካታች የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ሁላችንም ቃል መግባት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም