ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ የአፍሪካና ህንድ ትብብርን ለማጎልበት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ የአፍሪካና ህንድ ትብብርን ለማጎልበት እየሰራች መሆኗን የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለፁ። 

በአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (AUDA-NEPAD) እና ማሕበራዊ እና የልማት ለውጥ ማዕከል (CSEP) አማካኝነት የተዘጋጀ የአፍሪካ ሕንድ የልማት መሪ እቅድ ሪፖርት ይፋ ሆኗል። 


 

የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት አድጓል። 

ይህም ከሁለቱን ሀገራት ባለፈ የአፍሪካ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል። 

ዛሬ ይፋ የተደረገው መሪ እቅድም የአፍሪካና ሕንድ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን አንስተው፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ትብብርን እንደሚያጎለብት ገልፀዋል። 

የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህም ዓለም እንደ አንድ ቤተሰብ ናት ከሚለው የሕንድ እሳቤ ጋር የተሰናሰለና የአፍሪካና ሕንድ ትብብርን የሚያጎለብት ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በፋይዳ መታወቂያና በመሶብ ማዕከላት ዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ መሪ እቅዱ የሕንድና አፍሪካ ትብብር  በዲጂታል፣ በትምህርት የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል። 


 

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር እና የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ መልዕክተኛ አኒል ኩማር ራይ በበኩላቸው፤ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር  ያላት ግንኙነት የሀገራት ሉዓላዊነትን ያከበረና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም