ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የድንገተኛ በሽታዎች የመከላከል አቅም ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የድንገተኛ በሽታዎች የመከላከል ሀገራዊ አቅም ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ። 

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር በተደረገው ርብርብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት፤ በተቀናጀና ፈጣን የበሽታ መከላከል ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሽታውን የተቆጣጠረችበት ውጤታማ ተግባር ዜጎች ከተባበሩ ማሳካት የሚሳናቸው ነገር እንደሌለ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ድንገተኛ በሽታ የመከላከል ሀገራዊ አቅም ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።

የማርበርግ ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት በተከናወነው ስኬታማ ሥራዎች የጤና ሙያተኞች ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን ምጣኔን በማሻሻል አስተማማኝ የጤና ሥርዓት መገንባት የሚያስችሉ ትልልቅ ሀገራዊ ግቦች ተቀርጸው እየተሰራባቸው መሆኑን አንስተዋል።

ለጤና አገልግሎት የሚውሉ የሕክምና መድኃኒትን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ውጤታማ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት ለጤና ሥርዓቱ አቅም የሚሆኑ ትምህርቶች ተገኝተዋል።

በቀጣይም ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትን አጠናክሮ በማስቀጠል ምላሽ አሰጣጥ ስርዓቱን የሚያጠናክሩ የምርምር ሥራዎችን ለማስፋት እንደሚሰራበት አረጋግጠዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሙያተኞች፣ የጤና ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለድርሻ ተባባሪ አካላት ዕውቅና የሚሰጣቸው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም