ቀጥታ፡

በክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪው ስኬታማ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር)

ቡታጅራ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪው ስኬታማ  እንዲሆን ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

በክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ "አምራች ኢንዱስትሪ የሉዓላዊነትና የብልጽግና መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስኬታማነት በትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተግባራዊ በማድረግ የዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን በመፍታት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት  የሚደረጉ ጥረቶች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ባለሀብቶችም ለልማት የተረከቧቸውን መሬቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ የዘርፉን ስኬት ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ኢንቨስትመንትን የመሳብና በዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በበለጠ በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በተሰጠው ትኩረት ከብድር አቅርቦት ጀምሮ መሻሻል መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ወዲህ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ እድሎች እንዳሉት ጠቅሰው ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደገለፁት የኢንዱስትሪ ዘርፉን መደገፍ እንደ ሀገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት  ያግዛል፡፡

ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በሁሉም አካባቢ ለኢንዱስትሪ ዞን የሚሆን መሬት ለይቶ የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ስኬት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡


 

የክልሉ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሀመድ (ዶ/ር) በክልሉ በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከብድርና ከመሰረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በበለጠ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ተጋባዥ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም