ቀጥታ፡

ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በዘርፉ እድገት እየተመዘገበ ነው

ቡታጅራ ፤ የካቲት 2/2018(ኢዜአ) ፡-መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በዘርፉ ፈጣን እድገት እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ፡፡ 

"አምራች ኢንዱስትሪው የሉዓላዊነትና የብልጽግና መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል፡፡ 


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እየተደረጉ ያሉ ማበረታቻዎች  ዘርፉ ፈጣን  እድገት እንዲያስመዘገብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡

በክልሉ  በ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በውጭ ባለሀብት ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘውን የብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

ግንባታው ለበርካታ ዜጎችም የስራ እድል መፍጠር መቻሉም በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉንም ነው የተናገሩት።

ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ ግብዓት በመጠቀምና እሴት በመጨመር ምርቱን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ይህም የክልሉን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ፈጣን እድገት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው ያስረዱት፡፡

በክልሉ ለግል ባለሀብቱ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግም ለግል ባለሀብቱ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የኢንቨስትመንት መሬትን ጨምሮ የግብርና ግብዓት የማዘጋጀት ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሚኒስቴሩም ለዘርፉ ስኬታማነት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ነው ያረጋገጡት፡፡


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ የሚያደርግ እምቅ አቅም መኖሩን  ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሁለንተናዊ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና ለማጠናከር ያለው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ነው የጠቀሱት።

በአሁኑ ወቅትም የገጠር ኢንዱስትሪን ከማስፋፋት ጀምሮ በቴክኖሎጂ የተደገፍ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ የሚጠበቀውን አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን እንደገለፁት፤ በዞኑ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ 272 ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተዋል ብለዋል፡፡


 

በዚህም ከ15 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ስለመቻሉም አመልክተው በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው  የገለጹት፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም