የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ሁኔታ ቀያሪ ዕዝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ሁኔታ ቀያሪ ዕዝ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፡-የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሰርጎ ገቦችና ሽብርተኞችን ተከታትሎ በመደምሰስና ሴራቸውን ቀድሞ በማክሸፍ ከውስጥም ይሁን ከውጪ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ሁኔታ ቀያሪ ዕዝ መሆኑን አዛዡ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ አስገነዘቡ።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ የዕዙን 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ የምሥረታ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ከየካቲት 7 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
በአከባበሩ ወቅትም ዕዙ ባለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ያስመዘገባቸው ድሎች ይዘከራሉ ብለዋል።
ዕዙ የሀገርን ሠላም በማስከበር ረገድ የነበረውን ጀግንነትና ወኔ ይዞ የቀጠለው የአሁኑ ትውልድም፤ ይህንኑ ገድል ለተተኪዎች እንዲያወርስና ያሉትን ጥንካሬዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል ነው ያሉት።
ኮማንዶ፣አየር ወለድና ልዩ ኃይል ፀረ-ሽብር በየሥርዓቱ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ያለፉና እየተጠናከሩ የመጡ ከመሆናቸውም በላይ የጠላትን ቅስም የሰበሩና ሀገርን ያኮራ ጀግንነት የፈጸሙ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሰርጎ ገቦችና ሽብርተኞችን ተከታትሎ በመደምሰስና ሴራቸውን ቀድሞ በማክሸፍ ከውስጥም ይሁን ከውጪ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ ሁኔታ ቀያሪ ዕዝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ዕዙ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የካቲት 7 ሐዋሳ ላይ በሚደረግ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
ከየካቲት 13 ቀን ጀምሮ ደግሞ የመጽሐፍና የዓርማ ምረቃ፣ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይና የፓናል ውይይት እንዲሁም በሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከበር አመላክተዋል።
የማይበገሩት ቀያይ ነብሮቹ በአየር፣በምድርና በውኃ ላይ የሚያቀርቧቸው የተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶችም የበዓሉ ድምቀቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አከባበሩ የካቲት 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሐዋሳ ስታዲየም ለየት ባሉ ዝግጅቶች በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።
የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች ፦
https://linktr.ee/ENADigital