ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስኬት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማላቅ በንግድ ሚዛን ላይ እመርታዊ ውጤት አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስኬት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማላቅ በንግድ ሚዛን ላይ እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍ ማብራሪያቸው÷ ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ48 በመቶ ያልበለጠ እንደነበር መግለጻቸውም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረት 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ይገባ የነበረን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እንደተቻለም አስታውቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተያዙ ዕቅዶች አኳያ 93 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የኢንዱስትሪ አፈፃጸም ስኬትም የበጀት ዓመቱን ጥቅል ዕቅድ በላቀ ጥራት ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በወጪ ንግድ፣ በተኪ ምርት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ሽግግር እመርታዊ ስኬት መመዝገቡን አስረድተዋል።

የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት ስኬትም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረውን ድርሻ ለማላቅ መሰረት እንደሚሆን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በፖሊሲ፣ በሕግና ስትራቴጂ ማዕቀፍ ዝግጅት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ስብራቶችን በመጠገን ለዘርፉ ማንሰራራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በሶስት ዓመታት ውስጥ የተቋማትና የዘርፉ ተዋናዮችን ቅንጅት በማጠናከር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠረው የማንሰራራት አቅም የምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነት በማሳደግ በሀገር ዕድገት ላይ ጉልህ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተኪ ምርት የተከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የንግድ ሚዛን በማመጣጠን የአምራቾችን የምርት መጠንና ጥራት ማስጠበቅ ያስቻለ ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ከወጪ ንግድ 149 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን በማስታወስ በ2018 በጀት ዓመት በስድስት ወራት የወጪ ንግድ 204 ሚሊየን ዶላር የላቀ ገቢ አስገኝቷል ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በጥራትና በመጠን በማላቅ በተኪ ምርትና ወጪ ንግድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እመርታዊ ስኬት መመዝገቡን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም