ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለደረሰው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለደረሰው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018(ኢዜአ)፦ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለደረሰው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን በንቁ ተሳትፎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሲሆን በዋናነት በሀገሪቱ ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ልዩነቶችን በማጥበብ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ነው።
እስካሁንም በአስራ አንድ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አካታችና አሳታፊ የአጀንዳ ማሰባሰብና ለዋናው ጉባኤ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ስራዎችን በስኬት አከናውኗል፡፡
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ምክር ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማንቃት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣ በአጀንዳ ማሰባሰብ፣ በተሳታፊዎች ልየታ እንዲሁም በሌሎችም ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም መሰረት በርካታ ስራዎች በጋራ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የምክክሩ አካታችነት በተግባር መረጋገጡን ጠቅሰው የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያንና ምሁራን እንዲሁም የሁሉም ተሳትፎ የተረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክከሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቁመው ስኬታማ ሆኖ እንዲካሄድም ምክር ቤቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይትና በሀሳብ የበላይነት ወደ ሚመራ ስልጡን የፖለቲካ ባህል ለማሸጋገር ትልቅ ዕድል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ሂደቱ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነት እንዲመክሩ በማድረግ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡