የበልግ አብቃይ የሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የበልግ አብቃይ የሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል
አዳማ ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦በአብዛኛው የበልግ አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያ ግምገማና የበልግ ወቅት ትንበያ ይፋ ማድረጊያ መድረክ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ማካሄድ ጀምሯል።
ኢንስቲትዩቱ በዚሁ መድረክ ላይ ይፋ እንዳደረገው የበልግ ወቅት የአየር ትንበያ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።
በዚሁ መሰረት የቦረና እና ጉጂ ዞኖች ፣ሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።
እንዳሁም የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል እና የምእራብና ደቡብ ምእራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ከሚገኙ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በሰሜን ምእራብ በመካከለኛው፣ በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይም መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራል።
በሌላ በኩል የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት መጠን በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን ምእራብ እና በደቡብ ምእራብ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የበልግ ወቅት የዝናብ አጀማመር በደቡብ አጋማሽ አካባቢዎች ላይ ቀደም ብሎ የሚጀመር ሲሆን በአወጣጥ ረገድ ግን በተወሰኑ ቀናቶች ዘግይቶ ይወጣል ተብሏል።
ይህን የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ መጠቀምና በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ እና ሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን ያስፈልጋል ተብሏል።
በዘንድሮ የበልግ ወራት የዝናብ መጠንም ለግብርና ስራ አመቺ መሆኑ ተገልጿል።