ቀጥታ፡

በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የሚያሳይ የፎቶ አውደ -ርዕይ ተከፈተ

ቡታጅራ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ ተከፈተ።

ዓውደ ርዕዩ "አምራች ኢንዱስትሪ የሉዓላዊነትና የብልጽግና መሰረት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ ፎረም ምክንያት በማድረግ በቡታጅራ ከተማ ተከፍቷል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እና የኢንዱስትሪ  ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አውደ ርዕዩን መርቀው ከፍተዋል።

በፎቶ አውደ ርዕዩ በክልሉ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

እንዲሁም በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ አስተዳደር በ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ግንባታ ስራ ተጎብኝቷል፡፡


 

በውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ግንባታ ስራ ከ75 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ አመት ተጠናቆ የማምረት ስራ እንደሚጀምርም ተመልክቷል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ለ369 ቋሚና ከ 5ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉም ተጠቁሟል፡፡


 

ፋብሪካው ከውጪ የሚገባውን ምርት  በመተካት  የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ ወደ ውጪ በመላክ የምንዛሪ ግኝት መጠንን እንደሚያሳድግ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም