ኢትዮጵያ በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ በማጠናከር ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበች መሆኗን በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶስ ገለጹ።
የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው የአዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ ጉዞ የሚያስደንቅ መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶስ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በፈጣን ስኬት የታጀበ ታሪካዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው።
ለብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ ትኩረት በመስጠት የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ክፍት ማድረጓም የግሉን ዘርፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ተቃርባለች ያሉት አምባሳደሩ÷ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከምትገኘው ኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመስራታችንም ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተመዘገቡ አስደናቂ የልማት ስኬቶች ከተማዋን ዘመናዊ ገጽታ እያላበሷት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የዲፕሎማሲ መግቢያ በር ናት ያሉት አምባሳደሩ÷ በቀጣይም የኢትዮ-ብራዚልን የንግድና ፖለቲካ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ አስረድተዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ የምታደርገው ዝግጅት የአባል ሀገራት መሪዎች የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የሚገነዘቡበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበባን በማስዋብ ዘመናዊና የበለጸገች ከተማ ለመገንባት ያከናወናቸው ሥራዎች የአህጉሪቷን መሪዎችን ጭምር የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፈጣን የልማት ሥራዎች የበለጸጉ የዓለም ዋና ዋና ከተሞችን የዕድገት መንገድ የተከተሉና ከተማዋን የሚያዘምኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
የዲፕሎማሲ ሥራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ ድልድይ ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ ለዚህም የኢትዮ-ብራዚል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በኢትዮ-ብራዚል መካከል የሚደረገው የቀጥታ የአየር በረራ አገልግሎትም የሁለቱን ሀገራት ዜጎች የእርስ በእርስ ግንኙነት እያጠናከረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።