ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ የልማት ጉዞ ለማሳካት የአየር ንብረት መረጃዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ይገባል

አዳማ ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ የልማት ጉዞ ለማሳካት የአየር ንብረት መረጃዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያ ግምገማና የበልግ ወቅት ትንበያ ይፋ ማድረጊያ መድረክ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ ማካሄድ ጀምሯል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን አስተማማኝነትና ቅልጥፍና በማሳደግ ሁለንተናዊ ልማትን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እየተወጣ ነው።


 

የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎቹ ለግብርና፣ ለውሃና ኢነርጂ፣ ለትራንስፖርት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለአደጋ አመራር፣ ለኢንሹራንስና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች በሳይንሳዊ መንገድ ተተንትነው መቅረባቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ለውሳኔ ሰጪዎችና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ  የጀመረችውን ሁሉን አቀፍ የልማት ጉዞን ለማሳካት የአየር ንብረት መረጃዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል  እንደሚገባም አማካሪው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር  ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ  ከአየር ሁኔታና ፀባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን  መረጃዎች በየወቅቱ  ለተጠቃሚዎች እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


 

የበጋ፣ የበልግ፣ የክረምት የአየር ሁኔታና ፀባይ ትንበያዎችና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎቶች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በማዋል  ውጤት ማስገኘታቸውን አንስተዋል።

የበጋ ወቅት የአየር ሁኔታ በጊዜና በቦታ ትንበያ ከክስተቶች ጋር  በእጅጉ የተጣጣመ መሆኑን አስረድተዋል።

በዛሬው መድረክም የአገራችን  የበልግ ወቅት ዝናብ  አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖን ለመቋቋም ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡም በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በሚገባ በመከታተል ጥቅም ላይ  ማዋል እንደሚገባው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም