ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2018 (ኢዜአ):- የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ ቁልፍ ሚና መጫወቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኢኮኖሚን አስመልክቶ የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሳዑዲ አረቢያ አሉላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ኮንፍረንሱ የተዘጋጀው በሳዑዲ አረቢያ የፋይናንስ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የጋራ ትብብር ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በኮንፍረንሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ለዘላቂ እድገት ያላቸውን ቁልፍ ሚና በተለይም የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ ልምዶች በማንሳት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

ኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት ከነበራት የበለጠ እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝና እ.አ.አ በ2025/26 ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

በኮንፍረንሱ የፋይናንስ ሚኒስትሮች፣ የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች እና በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የሚገኙ የዓለም መሪዎች ተሳትፈዋል።

የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት፣ የገበያ ሁኔታና ዓለም አቀፍ ትስስር ላይ እየመከሩ ይገኛል።

https://linktr.ee/ENADigital

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም