ቀጥታ፡

በተጠባቂው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ሊቨርፑልን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፦‎ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር  ማንችስተር ሲቲ ከመመራት ተነስቶ ሊቨርፑልን 2 ለ 1 አሸንፏል።



ማምሻውን በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዶምኒክ ስቦዝላይ በ74ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ ቀያዮቹ መሪ ሆነዋል።

በርናንዶ ሲልቫ በ84ኛው ደቂቃ በጨዋታ እና አርሊንግ ሃላንድ በ93ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት የማንችስተር ሲቲን የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።



በጨዋታው ላይ ለሊቨርፑል ግቧን ያስቆጠረው ዶምኒክ ስቦዝላይ በ103ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ሃላንድ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 21 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አጠናክሯል።

በጨዋታው ማንችስተር ሲቲ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድል በመፍጠር የተሻለ ነበር።

በሊጉ 15ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ሲቲ ነጥቡን ወደ 50 ከፍ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ብሏል። በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ39 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ዛሬ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ በኢስማይላ ስር ግብ ብራይተንን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ተጠናቋል።

የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከየካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም