ቀጥታ፡

በገጠር አካባቢዎች በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

ጭሮ ፤የካቲት 1/2018 (ኢዜአ) ፦መንግስት  በገጠር አካባቢዎች በፀሀይ ሀይል  የሚሰሩ  የኤሌክትሪክ  አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቡርቃ ዲንቱ ወረዳ የተገነባ የፀሐይ ሀይል  ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጄክት ተመርቋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሱልጣን  ወሊ  እንዳሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን  ለማሳካት  ለአማራጭ የሀይል ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቷል።

መንግስት በተለይም  በገጠር አካባቢዎች በፀሀይ ሀይል  የሚሰሩ  የኤሌክትሪክ  አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

ለአብነትም ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ክልሎች የተገነቡ  የፀሀይ ሐይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች  የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም በአካባቢው የሚገነቡ አማራጭ የኤሌክትሪክ ሀይል  ፕሮጄክቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ እና የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ብርሀኑ በበኩላቸው የፀሐይ ሐይል ፕሮጄክቶቹ ለገጠሩ ህብረተሰብ ከመኖሪያ ቤት  በተጨማሪ  ለመንግስት መስሪያ ቤቶች በተለይም  ለጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

በዛሬው ዕለትም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቡርቃ ዲንቱ ወረዳ የተገነቡት ሁለት የፀሐይ ሀይል ፕሮጀክቶችም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን   አመልክተዋል።

የቡርቃ ዲንቱ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሽም ቡሹራ በበኩላቸው የፀሀይ ሀይል ማመንጫ  ፕሮጀክቶቹ  የገጠሩን ህብረተሰብ አኗኗርና የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዎ አላቸው።

ፕሮጀክቶቹ  ለገጠሩ ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ሀይል ከማዳረስ ባለፈ የትምህርትና ጤና ተቋማትን አገልግሎት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም