ቀጥታ፡

በክልሉ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ጨምሯል

ጎንደር፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- በጤና ተቋማት የሚወልዱና የጤና ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።

“ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ የቆየው የጤናማ እናትነት ወር ክልል አቀፍ የማጠቃለያ መርሐ-ግብር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
 
በዚሁ ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትሜ፤ በወሊድ ወቅት እናቶች የሚገጥማቸውን ሞት ለመቀነስ የሚያግዙ የቅድመና የድኅረ ወሊድ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ቀድሞ ከነበረው በላይ ማመቻቸት መቻሉን ገልጸዋል።  



 
በዚህም 76 በመቶ ለሚሆኑ እናቶች በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አረጋግጠዋል።

በደም መፍሰስ የሚገጥመውን ሞት ለመቀነስም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 44 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን አመላክተዋል።

በክልሉ 933 ጤና ተቋማት ለእናቶችና ለጨቅላ ሕጻናት የተሟላ የጤና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም 322 የጤና ተቋማት የአልትራ ሳውንድ የምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
 
እናቶች ወደ ጤና ተቋም ለወሊድ ሲመጡ እንዳይቸገሩ 632 የእናቶች ማቆያዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው፤ ይህም በጤና ተቋም እንዲወልዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያስረዱት።
 
 በተሠራው ሥራም በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ያስቻለ ውጤት መገኘቱን ነው ያረጋገጡት።
 



እናቶች በሰለጠኑ ባለሙያዎች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ያስረዱት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ ናቸው።

የእናቶች ወር መከበርም እናቶች ተገናኝተው ስለ ጤና ሁኔታቸውና ስለ አኗኗራቸው በመወያየት ግንዛቤያቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል መፍጠሩን አስገንዝበዋል።


 

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው፤ መንግሥት የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም