ለእንግዶች ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት አድርገናል - ሆቴሎች - ኢዜአ አማርኛ
ለእንግዶች ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት አድርገናል - ሆቴሎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):-በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለሚታደሙ እንግዶች ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች አስታወቁ።
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሕብረቱ የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የካቲት 4 እና 5/2018 ዓ.ም በመሪዎች ደረጃ የካቲት 7 እና 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሂድ ይሆናል።
የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤም ''ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የሚል መሪ ሃሳብ ተሰጥቶታል።
ኢትዮጵያም የሕብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በስኬት ማስተናገድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
የአዲስ አበባ የሆቴል ተቋማትም በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለሚታደሙ እንግዶች አስፈላጊውን የመስተንግዶ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የካሲዮፒያ ሆቴል ማናጀር ጌታቸው ጎበዜ፤ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ላይ ለሚታደሙ እንግዶች ጥራት ያለው መስተንግዶ የመስጠት ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ቀናት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለሚታደሙ እንግዶችም ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት የታከለበት አገልግሎት ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ እስጢፋኖስ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የመሠረተ ልማት ስኬቶች የሀገርን ገፅታ በመግለጥ ለሆቴል ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ ምኅዳርን ፈጥረዋል ብለዋል።
በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት ለሚታደሙ እንግዶችም የአፍሪካዊያንን የጋራ እሴት የሚያንጸባርቅ ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል መስተንግዶ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
የሆቴል አገልግሎት የሀገርን ገጽታ በስፋት ማስተዋወቅ የሚያስችል የቱሪዝም ዘርፍ ነው ያሉት ደግሞ የራማዳ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ወንደሰን በቀለ ናቸው።
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለሚታደሙ እንግዶችም ምቹና ጥራቱን የጠበቀ የመስተንግዶ አገልግሎት ለማቅረብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አስቴር ሰለሞን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ለሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ አቅም የሆኑ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል።
የዘንድሮው 39ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤም መዲናዋ አስደናቂ የልማት ስኬት ማምጣት በቻለችበት ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ለዚህም የሆቴል ባለንብረቶች በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለሚታደሙ እንግዶች ሀገራዊና አህጉራዊ እሴትን የሚያንጸባርቅ ጥራት ያለው መስተንግዶ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡