ቀጥታ፡

አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለገጽታ ግንባታና ለኮንፍረንስ ቱሪዝም እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):-አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታና ለቱሪዝም ኮንፍረንስ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የማዕከሉ ምክትል ስራ አስኪያጅ ኪሩብኤል ከፍያለው ገለጹ።

አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።


 

የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክትል ስራ አስኪያጅ ኪሩብኤል ከፍያለው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማእከሉ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ ከ73 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች፣ ኤግዚብሽኖችና ሁነቶች ተዘጋጅተዋል።

በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ አፓርትመንቶች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።


 

በማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በብቃት መካሄዱን ጠቁመዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማዘጋጀት አቅም መጎልበቱን ገልጸው፣ ማእከሉ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራንም በማሳለጥ ያለውን ሚና ገልጸዋል።

በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ለኮንፍረንስ ቱሪዝም እንዲሁም ለገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሁነቶች አዘጋጅ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ዮአዳን ጥላሁን፤ በማዕከሉ ለሚዘጋጁ ስብሰባዎችና ሁነቶች ቀልጣፋና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ለኮንፍረንስ ቱሪዝም እድገት ሚናችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።

በማዕከሉ የባህል ምግብ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅ እሸቱ አለማየው የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎችን የሚስብ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል  40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ3 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትላልቅ አዳራሾች፣ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች በጠቅላላ እስከ 10 ሺሕ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አዳራሾችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን የያዘ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም