ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት የሃገር ሉአላዊነትንና የህዝብ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ ለትውልድ ግንባታ አሻራውን እያሳረፈ ነው

ሰቆጣ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም ከማስከበር ባለፈ ለትውልድ ግንባታ አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በሰቆጣ ያስገነባው ''ሰላም የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ሰማዕታት መታሰቢያ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት'' ተመርቋል።

ቤተ-መጻሕፍቱን የመረቁት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የቤተ-መጻሕፍቱ ግንባታ ዕውቀትን የታጠቀ ትውልድ ለማፍራት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሀገር ክብርና ለሉዓላዊነት መረጋገጥ አኩሪ ገድል እየፈጸመ ያለ የህዝብ ኩራት መሆኑንም ገልጸዋል።

ሰራዊቱ የህዝብን ሰላምና የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ ለተሻለ ትውልድ ግንባታ አሻራውን እያሳረፈ ነው ብለዋል።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ያስገነባው ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት ቴክኖሎጂና ዕውቀት የታጠቀ ትውልድ ለማፍራት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል።

ትውልዱ የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖረውና ለሀገር ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ሰራዊቱ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ነው የገለጹት።


 

ለዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ አስፈላጊው የሰው ሃይልና ግብዓት ተሟልቶ በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚደረግ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀኔራል ዘውዱ በላይ በበኩላቸው፣ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።


 

ሰራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ ትውልዱ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ታጥቆ የሀገሩን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግና የንባብ ባህሉን እንዲያዳብር ያግዛል ነው ያሉት።

ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ትልቅ አበርክቶ አለው ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ናቸው።


 

የሰራዊት አባላት ትውልድን በዕውቀት ለማነጽ ያስገነቡት ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት የሰራዊቱን የህዝብ አለኝታነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪው ክብሮም ማሩ የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍቱ ግንባታ ለአካባቢው ተማሪዎች ተጨማሪ ዕውቀት የሚያስይዝና ተወዳዳሪነታቸውን የሚጨምር መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም