የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት አሳድገዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):-በመዲናዋ የተገነቡ የኮሪደር ልማትና ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት ማሳደጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።
"ብስከሌትን በአዲስ" በሚል መሪ ሃሳብ የብስክሌት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ አራዳ ፓርክ እየተካሄደ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢንያም ታዬ ፤ የቱሪዝም ዘርፍ የዓለም ዋነኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኢንዱስትሪ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል ፈጠራ፣ ለውጭ ንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እና ጥቅል ሀገራዊ ምርት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱን ፈርጀ-ብዙ የቱሪዝም ሃብቶች በስፋት በማልማት ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማትና ወንዝ ዳርቻ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የዚሁ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የከተማውን ገጽታ የቀየሩና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ያሳደጉ ናቸው ብለዋል።
የብስክሌት ፌስቲቫሉ በየወሩ የሚከናወን መሆኑን አንስተው ዓለማውም ከተማዋ ያሏት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል።
በከተማዋ ኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ የተገነቡ ውብና ሳቢ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች ብስክሌትን እንደ አማራጭ የትራንስፖርት መገልገያነት ተጠቅመው መጎብኘት እንደሚቻል ለማስገንዘብ እንደሆነም አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ በበኩላቸው፤ በከተማዋ ሞተር አልባ ትራንስፖርት ለማስፋፋት እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መካከል የብስክሌት ትራንስፖርት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አካባቢ ተፈጥሯዊ ፣ ውብና ሳቢ ገጽታውን ጠብቆ እንዲቆይ ትልቅ አበርክቶ ያለው ነው ብለዋል።