ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የካዳርስተር ምዝገባ ዲጂታላይዝድ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የካዳርስተር ምዝገባ ዲጂታላይዝድ እየተደረገ ነው
ደብረ ብርሃን፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የካዳርስተር ምዝገባ ዲጂታላይዝድ እየተደረገ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ እታለማሁ ይምታቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማዋ የመሬት መረጃዎችን በማዘመን አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ እየተደረገ ነው ብለዋል።
መሬትን በካዳስተር ሥርዓት መመዝገብ ገቢን ከማሳደግ ባለፈ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከ7 ሺህ ለሚልቁ ባለይዞታዎችን ሕጋዊነት የማረጋገጥ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ይዞታቸው የተረጋገጠ ከ2 ሺህ 800 በላይ መሬቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማስገባት መቻሉንም ጠቁመዋል።
በከተማዋ የጠባሴ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ፈለቁ ጌታነህ እና ጌታነህ ሸዋፈራ እንዳሉት፤ ዘመናዊ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሕገ-ወጥነትን በመከላከል ፍትሐዊ አገልግሎት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።