ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል-ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል-ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዳማ፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፦ስፖርትን ለስነ ምግባር ግንበታና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለውን እቅም ለማሳካት ትኩረት መሰጠቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።
ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር "የተተኪ ስፖርተኞች ልማት፤ ለስፖርታችን እድገት" በሚል መሪ ሐሳብ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዛሬ ተጀምሯል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በወቅቱ ስፖርትን ለስነ ምግባር ግንባታና ተተኪዎችን ለማፍራት ያለውን አቅም ለማሳካት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ስፖርትን ለሀገር ገፅታ ግንባታና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ሚናን ለማጉላት እንዲቻል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትም የምልመላና ስልጠና ስርዓት ከመዘርጋት ጎን ለጎን ለስፖርት መሰረተ ልማት ተደራሽነት ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት 17 ሺህ 636 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በሀገሪቷ ተገንብተው ለታዳጊዎች የአካልና የአእምሮ ብቃት ማጎልበቻ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል።
ዛሬ በአዳማ የተጀመረው ውድድርም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሮዛ ቢያ እንደተናገሩት፥ ክልሉ ለስፖርት ልማት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ስልጠናዎችን እየሰጠ ነው።
የስፖርት ልማትን ለማሳካት የክልሉ ከተሞችና ወረዳዎች የስፖርት ማዘወተሪያዎችን ከኮሪደር ልማት ጋር በማቆራኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬም በ15 የስፖርት አይነቶች ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከ3ሺህ በላይ ታዳጊዎች በውድድር እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው ከተማዋን ለነዋሪው ምቹ ለማድረግ የስፖርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።
ታዳጊዎች በአእምሮና በአካል ብቁ እንዲሆኑ የመዝናኛና ስፖርት ስፍራዎች በከተማዋ በስፋት እየተገነቡ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች ፦
https://linktr.ee/ENADigital