ምክክሩ በአጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጉልህ ጠቀሜታ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ በአጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጉልህ ጠቀሜታ አለው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሴቶችና ወጣቶች በሚያነሷቸው አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው የአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ማኅበራት አስገነዘቡ።
የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት እናትዓለም እንዳለ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በዜጎች መካከል የውይይት መድረክ በማካሄድ አለመግባባቶችን በጸና ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚተካ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማኅበራቸው በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረኮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉንም አስታውቀዋል።
በቀጣይም ለሀገራዊ ምክክሩ በቀረቡ አጀንዳዎች መነሻነት በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ ሴቶችን የተመለከቱ አጀንዳዎችን በመለየት ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት በረከት ብርቢርሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ዕድል ነው ብለዋል።
በቀጣይም በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ የነበራቸውን ተሳትፎ በማስቀጠል ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሀገርን ማዕከል በማድረግ የሴቶችና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችሉ መስኮች ላይ በትኩረት እንደሚሠሩም ፕሩዚዳንቶቹ ለኢዜአ ገልጸዋል።