ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር የአኗኗር ዘይቤ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- የገጠር ኮሪደር ዘመናዊ የቤት ባለቤት በማድረግ ምቹ የአኗኗር ዘይቤ እንደፈጠረላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር ባለሃብቶችን በማስተባበር በምዕራብ ሸዋ ዞን ያስገነባቸውን ዘመናዊ ቤቶች ገንብቶ ለአርሶ አደሮች አስረክቧል።


 

የመኖሪያ ቤቶቹ መንግሥት የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የተገነቡ ናቸው።

የፀሐይና ባዮ ጋዝ የኃይል አማራጭ፣ ምቹ የእንስሳት በረት እንዲሁም አንድ የመኖሪያ ቤት ሊያሟላቸው የሚገቡ የቤት ቁሳቁስና አገልግሎቶችን ያሟሉም ናቸው።


 

የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አርሶ አደሮችም፤ የገጠር ኮሪደር ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶቹ የኑሮ ዘይቤያቸውን በመቀየር ምቹ የመኖሪያ ከባቢ እንደፈጠሩላቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።


 

በዞኑ የደንዲ ወረዳ ነዋሪ ሌንሴ ደበሌ፤ ከዚህ ቀደም የነበራቸው ደሳሳ ጎጆ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር በዝናብ ምክንያት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በሞት ካጧቸው ባለቤታቸው ካፈሯቸው አምስት ልጆቻቸው ጋር በደሳሳ ጎጆዋ ውስጥ በዝናብና በብርድ ጎስቋላ ኑሮን ለመምራት ተገደው መቆየታቸውንም ያወሳሉ።

በተሻለ ጥራት ተገንብቶ የተሰጣቸው የመኖሪያ ቤትም ያሳለፉትን አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ በመቀየር ምቹና እፎይታን የቸረ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ የሚመሩበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።


 

በምዕራብ ሸዋ ዞን የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ነዋሪ ዳማሳ ሆርዶፋ በበኩላቸው ጧሪና ደጋፊ እንደሌላቸው በመጥቀስ፤ መኖሪያ ቤታቸው አርጅቶ ከላያቸው ላይ ሊፈርስ ተቃርቦ እንደነበር ገልጸዋል።

የተበረከተላቸው ሁሉም ነገር የተሟላለት ዘመናዊ የመኖሪያ ቤትም፤ የማምሻ ዕድሜያቸውን ከጨለማ ወደ ብርሃን የለወጠ ምሥጋና የሚቸረው አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው በደስታ ተናግረዋል።


 

የተበረከተላቸው የመኖሪያ ቤት ንጹህና ሁሉንም መሠረተ ልማቶች ያሟሉና ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን ያጎናጸፉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ በዞኑ ደንዲ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርፋሴ ፊጣ ናቸው።


 

በዞኑ ኤጀርሳ ለፎ ወረዳ ነዋሪዋ ብርቄ ፉፋ በበኩላቸው፤ የገጠር ኮሪደር ጎስቋላ ኑሯቸውን በመቀየር ምቹ ሁኔታ የአኗኗር ዘይቤን የሚመሩበት አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ገንብተው ላበረከቱላቸው ተቋማትና ግለሰቦች ምሥጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም