ለሌማት ትሩፋት በተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለሌማት ትሩፋት በተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል
ሐረር፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል ለሌማት ትሩፋት በተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።
የሐረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሶፊ ወረዳ በርቃ ቀበሌ እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ በዚሁ ወቅት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት በሐረሪ ክልል ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ በወተት፣ እንቁላል፣ በዶሮና ማር ምርት በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም አስታውቀዋል።
በተለይ የላሞችን ዝርያ በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ማሻሻልን ጨምሮ የሥጋ እና ማር ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ ለሌማት ትሩፋት ትኩረት በመስጠት በተሠራው ሥራ የተመዘገበው ውጤት በቤተሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት መሠረት መሆኑን አመላክተዋል።
በሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ የማር እና ዶሮ መንደር መመስረታቸውን ገልጸው፥ በተጨማሪም የወተት መንደር ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንና እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።