ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ሐረር፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ከጊዜ ከወደ ጊዜ ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ገንዘብ ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው የበጀት ዓመቱን ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ መሐመድናስር አባጀማል (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መከናወናቸውን አረጋግጠዋል።

ከነዚህም መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የዐቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት፣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስና የማጠናከርያ ትምህርት፣ የመንገድ ግንባታ፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታና የመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ ነጻ የጤና ሕክምና፣ ሞዴል ፋርማሲና ሌሎች ተግባራትን ጨምሮ 72 ዓይነት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በተግባራቱም የክልሉ ነዋሪ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ በሕዝብ ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስገንዝበዋል።


 

መንግሥት ለማኅበረሰቡ ልማት ምቹ ሁኔታን ከፈጠረ፤ ሕዝቡ ማሳደግና መጠቀም እንደሚችል ተምሳሌታዊ ሥራን አሳይቷል ሲሉም አስረድተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የመደጋገፍና የአብሮነት ባህልን እያሳደገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም