ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተመዘገቡ የልማት ሥራዎች ለሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ድምቀት ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተመዘገቡ አስደማሚ የልማት ሥራዎች ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ተደማሪ ድምቀት መሆናቸውን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ከተማዋን ለነዋሪምቹ ከማድረጋቸው ባለፈ የአፍሪካ መዲናነቷን እያረጋገጡ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።


 

ከነዋሪዎች መካከል ዘሪሁን ግሩም እንዳሉት፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም ቀደም ሲል የነበረው የከተማዋ ገጽታ ስሟን የሚመጥን አልነበረም። 
 
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎቿ ምቹ ከመሆን ባለፈ ለአፍሪካም አርአያ የሚሆኑ ተግባራት መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እና የመላ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል መሆኗን የገለጹት እንዳሻው ፍቃዱ፤ በዕድገት እና በልማትም ግንባር ቀደም መሆኗም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል


 

የልማት ሥራዎቹ የሀገርን ክብር ከፍ ከማድረጋቸው ባለፈ የዜጎችን ኑሮ የሚቀይሩ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ የገለጹት ደግሞ አየለ አንጀሎ እና ሙሉቀን ተስፋዬ ናቸው።


 

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከየካቲት 7 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም