ፒኤስጂ እና ማርሴይ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
ፒኤስጂ እና ማርሴይ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):- በፈረንሳይ ሊግ አንድ 21ኛ ሳምንት ፒኤስጂ ከማርሴይ ይጫወታሉ።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ከ45 በፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም ይካሄዳል።
ፒኤስጂ በ48 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ማርሴይ በ39 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የፓሪሱ ክለብ ፒኤስጂ በሊጉ 20 ጨዋታዎችን አድርጎ 15ቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ20 ጨዋታዎች 43 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 16 ጎሎችን አስተናግዷል።
ተጋጣሚው ማርሴይ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 20 ጨዋታዎች መካከል በ12ቱ ድል ሲቀናው አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀስታ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።
46 ግቦችን ሲያስቆጥር 22 ተቆጥረውበታል።
ማርሴይ በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን ነው።
ሁለቱ ክለቦች በፈረንሳይ ሊግ 1 ሲገናኙ የዛሬው ለ45ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 44 ጨዋታዎች ፒኤስጂ 26 ጊዜ ሲያሸንፍ ማርሴይ በ10ሩ ድል ቀንቶታል። ስምንት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ፒኤስጂ አራትት ጊዜ ሲያሸንፍ ማርሴይ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ "Le Classique" የሚል ስያሜ አለው።
የሁለቱ ቡድኖች ከእ.አ.አ 1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ታሪካዊ ተቀናቃኝነት አላቸው።
ፒኤስጂ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የሚገኝ እና የሀብታሞች ከተማ እየተባለ ይጠራል።
የወደብ ከተማ የሆነችው ማርሴይ የሰራተኛ ማህረሰብ የሚኖርባት እና በከተማቸው ጉዳይ ወግ አጥባቂ የሚባሉ ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ ናት።
ይህ ከእግር ኳሱ ባለፈ የፖለቲካና የኢኮኖሚው ጉዳይ ተቀናቃኝነቱን የበለጠ አጋግሎታል።
ፒኤስጂ የፈረንሳይ ሊግ አንድ 13 ጊዜ አሸንፏል። ባለፉት ዓመታት በሊጉ የበላይነቱን ይዟል።
ክለቡ የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ነው።
ተቀናቃኙ ማርሴይ ዘጠኝ ጊዜ ሊጉን ማሸነፍ ችሏል። የሊግ ውድድሩን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው እ.አ.አ 1988/89 የውድድር ዓመት ነው።
ሁለቱ ክለቦች የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ያነሱ የፈረንሳይ ክለቦች ናቸው። ፒኤስጂ የወቅቱ የውድድሩ የዋንጫ ባለቤት ነው።
የዛሬው ጨዋታ ፒኤስጂ መሪነቱን ከሌንስ ለመረከብ፣ ማርሴይ በአውሮፓ መድረክ የመሳተፍ ህልሙን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊግ ጨዋታ ማርሴይ በናይፍ አገርድ ግብ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የ33 ዓመቱ ዊሊ ዴላጆድ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የዘንድሮው የፈረንሳይ ሊግ 1 ክስተት የሆነው ሌንስ በ49 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።