ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018 የግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018 የግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ተካሄደ
ሀዋሳ ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):-ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018 የግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ተካሄደ።
ከአንኮበር እስከ ሀረር በሚል የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018 የሩጫ ውድድር በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል።
በሀዋሳ ሃይቅ ዳርቻ ዛሬ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር የአዲስ አበባ ፖሊስ አትሌቶቹ ስማቸው ወልዴ ወንዶች እና ቤተልሄም አስማረ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል።
በወንዶች በግል የተወዳደሩት አትሌት ጌታቸው ኪዳኔ እና ሱልጣን አብደላ በቅደም ተከተል 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።
በሴቶች ትነበብ ነጋ ከአዲስአበባ ፖሊስ፤ ያተኔ ኮሞሼ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።
በግማሽ ማራቶን ከተደረገው የሁለቱም ጾታ አትሌቶች ውድድር በተጨማሪ በአንጋፋ አትሌቶች፣ እንዲሁም በታዳጊዎችና በህጻናት የአራት ኪሎሜትርና የአዋቂዎች የ8 ኪሎሜትር ውድድር ተከሂዷል።
ከአትሌቶች አንደኛ ለወጡት የ100 ሺህ ብር፤ ለሁለተኛ 50ሺህ ብር፤ ሶስተኛ ለወጡት የ15 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ከአንኮበር እስከ ሀረር በሚል እየተካሄደ ያለው የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክ 2018 የሩጫ ውድድር በቀጣይ በጅማ፣ አርባምንጭ፣ በቆጂና ሀረር ከተሞች እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በኢትዮ ቴሌኮም ስያሜ የተካሄደው የሀዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን ውድድር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።