በነቀምቴ ከተማ በጎጆ ኢንዱስትሪ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ በጎጆ ኢንዱስትሪ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው
ነቀምቴ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):- በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ በጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገለጹ።
ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውጤታማ በመሆናቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በከተማዋ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ ለጥቅም በማዋል ስራ ላይ የተሰማራው የአመዩ እና ፍንታዬ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አመዩ ደረጄ በተደራጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል።
ማህበሩ ከመንግስት ባገኘው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብድር ጥቅም ላይ የዋሉ ፕላስቲኮችን መልሶ በማምረት ለተለያዩ አገልግሎቶች ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል ብሏል።
ወጣት አመዩ አክሎም ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ማምረት እንዲችሉ መንግስት የሚያመቻቸውን የብድር፣ የመስሪያ ቦታ እንዲሁም ስልጠናና ድጋፍ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አመልክቷል።
ማህበራቸውም በዚህ አመት በመደራጀትና ጠንክሮ በመስራት ባስመዘገበው ውጤት ለሌሎች 14 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁሟል።
የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ደራርቱ ገቢሳ በአሁኑ ጊዜ ባገኘቸው የስራ እድል በወር ከ6ሺህ 500 ብር በላይ በማግኘት እየሰራች መሆኗን ገልፃለች።
ወደፊትም በሚደረጉ ድጋፎች እና በምታገኘው የስራ ልምድ ራሷን ችላ ለመስራት ማቀዷን ገልፃለች።
ሌላው ሰኚ፣ አዱኛ፣ ኩለኒ እና ጓደኞቻቸው የሽርክና ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ሰኚ ጋዲሳ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የብድር አቅርቦት በእንጨት ስራ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።
በማህበሩ ስር ለአስር ወጣቶች የስራ እድል መከፈቱን አንስቶ ወደ ፊት ስራውን በማስፋት በርካታ ወጣቶችን በስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ተግተን እንሰራለን ነው ያለው።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ብርሃኑ አሰፋ በከተማዋ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት በተያዘው እቅድ ውጤታማ የሆኑ ስራዎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
በተያዘው በጀት አመትም 79 ማህበራትን በማደራጀትና 121 ሚሊዮን ብር በማበደር በተለያዩ ስራዎች ላይ ማሰማራት መቻሉን ገልጸዋል።
ወጣቶች አዳዲስ የስራ ሀሳቦችን በማመንጨትና ተደራጅተው በመስራት ለከተማዋ እና አካባቢው ነዋሪዎች ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ከሚገኙ የጎጆ ኢንዱስትሪ ስራዎችም የሚስማር ማምረቻ፣ የልብስ ስፌት፣ የእንጨት መሰንጠቂያ፣ የብሎኬት እና ቴራዞ ማምረቻዎችና ሌሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አቶ ብርሃኑ አክለውም በስራው ወጣቶችን ውጤታማ ከማድረግም ባለፈ የስራ ባህላቸውን በመቀየር በቀጣይ ለተሻለ ውጤት ማብቃት ትልቁ ዓላማችን ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ለወጣቶቹ የድጋፍ እና ክትትል ተግባራትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።