መንግስት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የልማቱ ተጠቃሚ እያደረገን ነው - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የልማቱ ተጠቃሚ እያደረገን ነው - ነዋሪዎች
ሀዋሳ ፤ የካቲት 1/2018(ኢዜአ):-መንግስት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በሲዳማና ኦሮሚያ ክልል ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በሲዳማና ኦሮሚያ ክልል የገጠር ቀበሌዎች የተከላቸውን የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከሰሞኑ አስመርቋል።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የለውጡ መንግስት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻችንን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል።
ከሰሞኑ በአካባቢያቸው የተመረቀው የጸሃይ ሃይል ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዳሸጋገራቸውና ሰፊ የስራ እድል ይዞ እንደመጣም ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ የመሬራ ከተማ ነዋሪው አቶ አሰፋ ሆቶራ መንግስት የዜጎችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የትምህርት፣ የጤናና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ስለተሟሉላቸው አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
አካባቢያቸው ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የረዥም ጊዜ የመብራት ጥያቄያቸው ሳይፈታ መቆየቱን አስታውሰው፤ የጸሃይ ሃይልን በመጠቀም በቅርቡ የኤሌክትሪክ መስመር እንደተዘረጋላቸው ተናግረዋል።
ይህም የለውጡ መንግስት ለዜጎች የመሰረተ ልማት ጥያቄ አማራጭ መፍትሄ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የዚሁ ከተማ ነዋሪው አቶ ረጋሳ ቡሪሳ በበኩላቸው መንግስት ከገጠር እስከ ከተማ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው በተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ተጠቅመው ህይወታቸውን በሚቀይሩ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጡ መንግስት አማራጭ የልማት አውታሮችን በመዘርጋት ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ለአካባቢያቸው ለውጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ለበርካታ ዓመታት የኤሌክትረክ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በማገዶ ሲያበስሉ ጭስ እንደሚጎዳቸው የተናገሩት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ አርሲ ዞን የነንሰቦ ጨቤ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ቢርቂሳ መሃመድ ናቸው።
የነንሰቦ የጸሃይ ሃይል ማመንጫን ተከትሎ የተዘረጋው መስመር ብርሃን ከመስጠት ባሻገር ለምግብ ማብሰያነትና የተለያዩ ማሽነሪዎችን ለማንቀሳቀስ እያገዘ በመሆኑ መንግስትን አመስግነዋል።
የአካባቢው ህዝብ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየተመለሰ መሆኑን ጠቅሰው የውሃ፣ ጤናና ትምህርት መሰረተ ልማቶችን ለአብነት አንስተዋል።
ሌላኛው የነንሰቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሃመድሁሴን ከድር በበኩላቸው አካባቢው ከፍተኛ የቡና ምርት እንዲሁም ስንዴ እና ገብስ በብዛት የሚመረትበት መሆኑን ተናግረዋል።
ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ በመንግስት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸው በመሆኑ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የረዥም ጊዜ የኤሌክትሪክ ሃይል ጥያቄ በአማራጭ ኢነርጂ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸው አካባቢውን ለመለወጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ (ደ/ር) መንግስት ታዳሽ የኢነርጂ ሃይልን በመጠቀም ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለዜጎች ለማድረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
በመጪዎቹ ሁለት አመታትም ከ130ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ከ100 በላይ የጸሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እንደሚበቁ ተናግረዋል።
750ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉና በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ የቤተሰብ ሻማዎች እንደሚሰራጩና የጤናና የትምህርት ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትም እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።